‘’ኢትዮጵያ” የሚለው ስያሜ አመጣጥና ትርጓሜው
Table of Contents
‘’ኢትዮጵያ” የሚለው ስያሜ አመጣጥና ትርጓሜው
ኢትዮጵያ የሚለው ቃል መሰረቱ ‘’እንቆጳዝዮን” የሚለው ጥንታዊ የሳባ ቋንቋ ሲሆን በጊዜ ሂደት የሳባ ቋንቋ እየተተወ የግእዝ ቋንቋ በኢትዮጵያ በስፋት መነገር ሲጀምር ‘’ኢትዮጵግዮን’’ ተባለ ትርጎሙም ኢት ስጦታ፣ ዮጵ ቢጫ ወርቅ፣እንቁ ግዮን ፈሳሽ ወንዝ በአንድ ላይ ‘’የግዮን ወርቅ ስጦታ’’ የሚል ትርጓሜ የሚሰጥ ነው።
የኢትዮጵያ መጠሪያ ስም በተለያየ ጥንታዊ የነገስታት ዘመን የተለያየ ነበረ። ሰለዚህም በመጀመሪያ የኖህ የልጅ ልጅ በሆነው በ’’ኩሽ’’(የካም ልጅ) ስም ኩሽ ተብላ ትጠራ ነበር።
ቀጥሎ በናምሩድ ልጅ(የኩሽ የልጅ ልጅ) ‘’አቢስ’’ ‘አቢስኒያ’ ትባል ነበር።
ከዚያም በሳባኖባ ዘመን ‘’ኑብያ’’ ትባልም ነበር በዚህም ሳባኖባ የተባለውም በኖህ ዘር ውስጥ ሁለት ሳባ ሰለነበረ ነው 1ኛው የኖህ የልጅ ልጅ ኩሽ(የካም ልጅ) የወለደው ሳባ ነው ይህን ከሌላው ለመለየት ሳባ 1ኛ ወይም ሳባኖባ ይሉታል።
2ኛው ደግሞ የካም ወንድም የሴም የዘር ግንድ የሆነው የዮቅጣን ልጅ ሳባ ነው ይህን ደግሞ ሳባ 2ተኛ ወይም ‘’ሳባሻባ’’ ይሉታል ።
ከዚያም ከሴም ዘሮች ውስጥ ነገደ አጋዝያን ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ ደግሞ ከእነሱ አንዱ በሆነው በኢትዮጲስ 1ኛ ዘመነ መንግስት…. ኢትዮጵያ ተብላ ተሰየመች ።
እንደገና በየጊዜው ወደ ኢትዮጵያ በገቡት ነገደ ‘’ሃበሳ’’ን (በዛሬ ምእራብ የመን አከባቢ የሚገኙ በጥንት ጊዜ ከሃገራቸው ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የመጡ) ጊዜ ደግሞ በሳባውያን ፈደል ‘ሳ’ የነበረው በአረብኛ ‘ሳ’ ፈደል በ ‘ሻ’ ፈደል ተለውጣ ‘ሃበሻ’ የሚለው ስም እንደመጣ ይታመናል።
ሆኖም ግን ሃበሻ የሚለው ቃል በኢትዮጵያ በስፋት እየታወቀ የመጣው ቆይቶ በአክሱም ዘመነ መንግስት ነው። በአፍሪካ ቀንድ የመጀመሪያው ሃበሻ የሚለው ቃል ተጽፎ የተገኘው በ 4ተኛው መቶ ክፍለዘመን በንጉስ ኢዛና የንግስና ጊዜ ነው።
ፑንት፣ኑቢያ፣የሃበሻ ግዛት፣ አቢሲኒያ፣ኩሽ እነዚህ ሁሉ በተለያዩ መጽሃፋት ላይ ኢትዮጵያዊያንንና የኢትዮጵያን ግዛት የሚገልጹ ናቸው።
የኢትዮጵያ የመጀመሪያው መጠሪያ ስም፣መሰረቱ፣ምንጩ የቱ ነው?
ኢትዮጵያ በየለያዩ ጸሃፍት ዘንድ በተለያየ አጠራርና ስም ስትጠራ መኖሯ እንዳለ ሆኖ በዋናነት በኦሪት ላይ ‘’ኩሽ‘’ ተብላ ስፍራ እናገኛለን።
ከዚህ በኋላ 70 ሊቃውንት በጋራ ሆነው ብሉይን ከእብራይስጥ ወደ ጽርዕ/ግሪክ/ ሰተረጉሙ ‘’ኩሽ‘’ የሚለውን ቃል/ከግብጽ በስተደቡብ ያለውን አገር ሁሉ ለመጠቆም ይጠቀሙበት የነበረውን የነገድ አባት ስም/ ‘’ አይቶ ፒያ’’ ወይም ‘’Aithio – Pia’’ ብለው ቅ.ል.ክ 282 ላይ ተረጎሙት።
ይህንኑ ወደ ግእዝ ሲተረጉሙት ቃሉን ብቻ እንደወረደ ‘’ ኢትዮጵያ’’ ብለው አሰፈሩትና ከግእዝ ወደ አማርኛ ሲተረጎምም እንደገና ያለፍቺ ሆሄውን ብቻ በመውሰድ ሃገሯን ‘’ኢትዮጵያ’’፤ ህዝቡን ‘’ ኢትዮጵያዊ’’ አሉት።
ይህንንም ተመርኩዘው በርካታ የታሪክ ጸሃፍት ኢትዮጵያ የሚለው ቃል መሰረት ግሪክ ነው ትርጓሜውም ‘’ በጸሃይ የጠቆረ፣ በጸሃይ የተቃጠለ ፊት ያላቸው።’’ ብለው የውስዱታል። ይህም ከላይ እንዳየነው Aithio – Pia’’ ተብሎ ቅ.ል.ክ 282 ከተተረጎመው ትርጓሜ ላይ ‘’ አይቶ’’ ጥቁር፣ አቃጠለ የሚል ትርጉም ሲሰጥ ‘’ኦፕያ’’ ወይም ‘’ኦጵስ’’ ፊት የሚል ትርጓሜ ይሰጣል።
ይህ ትርጓሜ ልክ እንዳልሆነ የሚያሳየን የተለያዩ ማመሳከሪያዎች?
ራሱ የግሪክ ተወላጅ የሆነው ታላቁ ሆሜር በጻፈው እጅግ ተደናቂ በሆነው ኤልያድ/lliad/ እና ኦድሰይ(odyssey) ላይ
የአማልክት አባት ዜውስ ሃያላኑን ኢትዮጵያዊያንን ለማየትና አብሯቸው ምግብ ለመብላት ወደ ታላቁ ወንዝ ይወርዳል..። እያለ የተረከው ቅ.ል.ክ ከ1000 – 900 ባለው ጊዜ መካከል ነበር።
የኋለኛው ዘመን ግሪካዊ ሊቅ ሄሮደተስም ቅ.ል.ክ 490 ላይ የተወለደው
ስለዚህ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ከግሪክ የመጣ ላለመሆኑ ‘’ኢትዮጲስ 1ኛ’’ እና ‘’ኢትዮጲስ 2ኛ” የሚለው የነግስታት መጠሪያ ስም በቅደም ተከተል ከክርስቶስ ልደት በፊት 1856 – 1800 እና 1730 – 1700 በኢትዮጵያ የነገሱ ነግስታት በመሆኑ 70 ሊቃውንት የተረጎሙት መጽሃፍ ማለትም ኩሽ የሚለውን ወደ ግሪክ‘’ አይቶ ፒያ’’ በለው የተረጎሙትን ግን ከክርስቶስ በፊት 282 ላይ መሆኑ ኢትዮጵያ ከግሪክ የመጣ ነው የሚለውን ውድቅ ያደርገዋል።
እነ ንጉስ ኢትዮጲስ የአጋዚያን የነገስታት ዝርዝር ውስጥ ያሉ ናቸው የግእዝ ቋንቋ ደግሞ በአጋዝያን ዘመን ነበረ ፤ በግዕዝ የተጻፈ ሰነድም ሞልቷል። የአሃዝ ቁጥርም ነበራቸው፤ ኢትዮጵያ የሚለውም ቃል በግሪኮች ሳይታወቅ በፊት በኢትዮጵያ ነበረ ራሱን የቻለ ትርጉምም ነበረው።
‘’ኢት ስጦታ ፣ ዮጵ ቢጫ ወርቅ ወይም እንቁ ፣ ግዮን ፈሳሽ ወንዝ፣ በጥቅል ኢትዮጵግዮን ‘የግዮን ወርቅ ስጦታ ተብሎ በሱባ/በሳባ/ ይተረጎማል’’ /መጽሃፈ አብርሂት መሪ ራስ አማን በላይ 1999 አ.ም/
ኢትዮጵያ ማለት በአሁኑ አገላለጽ ‘’ኢት ዮጵ’’ያ የአማርኛ አባት በሆነው ግእዝ ‘’ኢትዮጳግዮን‘’
ቋንቋ ከመከፋፈሉ በፊት በኖህና በቤተሰቦቹ ዘመን ኩሽቲክ ሴሜቲክ ተብሎ ከመከፋፈሉ በፊት በነበረው የግእዝ አባት በሆነው በሳባ ቋንቋ በነበራት ስያሜ ‘’እንቆጳዝዮን‘’ የተባለች ሃገር ናት ።
በተደጋጋሚ የሚጠየቁ ጥያቄዎች
‘’ኢትዮጵያ” የሚለው ስያሜ አመጣጥና ትርጓሜው
ኢትዮጵያ የሚለው ቃል መሰረቱ ‘’እንቆጳዝዮን” የሚለው ጥንታዊ የሳባ ቋንቋ ሲሆን በጊዜ ሂደት የሳባ ቋንቋ እየተተወ የግእዝ ቋንቋ በኢትዮጵያ በስፋት መነገር ሲጀምር ‘’ኢትዮጵግዮን’’ ተባለ ትርጎሙም ኢት ስጦታ፣ ዮጵ ቢጫ ወርቅ፣እንቁ ግዮን ፈሳሽ ወንዝ በአንድ ላይ ‘’የግዮን ወርቅ ስጦታ’’ የሚል ትርጓሜ የሚሰጥ ነው።
ኢትዮጵያ ማለት በጸሃይ የጠቆረ፣ በጸሃይ የተቃጠለ ፊት ያላቸው ማለት ነው ?
አይደለም ምክንያቱም ራሱ የግሪክ ተወላጅ የሆነው ታላቁ ሆሜር በጻፈው እጅግ ተደናቂ በሆነው ኤልያድ/lliad/ እና ኦድሰይ(odyssey) ላይ
‘’ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ህዝቦች እጅግ ሃያላን እጅግ የሚያምሩና የተከበሩ ናቸው..’’ ይላል፤ መዝሙር ቁጥር 423 ላይ።
የአማልክት አባት ዜውስ ሃያላኑን ኢትዮጵያዊያንን ለማየትና አብሯቸው ምግብ ለመብላት ወደ ታላቁ ወንዝ ይወርዳል..። እያለ የተረከው ቅ.ል.ክ ከ1000 – 900 ባለው ጊዜ መካከል ነበር።
ዋቢ መጽሃፍትና ድህረ ገጾች
ፍስሃ ያዜ ካሳ። (2003 አ.ም)። የኢትዮጵያ የ5 ሺ አመት ታሪክ ከኖህ እስከ ኢህአዴግ መጽሃፍ 1። አዲስ አበባ፣ አልፋ አሳታሚዎች።
መሪ ራስ አማን። (1999 አ.ም)። መጽሓፈ አብርሂት።አዲስ አበባ፣
Homer. The Iliad with an English Translation by A.T. Murray, Ph.D. in two volumes. Cambridge, MA., Harvard University Press; London, William Heinemann, Ltd. 1924.
https://journals.bdu.edu.et/index.php/ejss/article/view/69/125
The Odyssey. Fagles, R.. New York,Viking., Penguin Books.1997.
https://department.monm.edu/classics/courses/clas240/Africa/homeronethiopians.htm
Herodotus, with an English translation by A. D. Godley. Cambridge. Harvard University Press. 1920.
http://www.perseus.tufts.edu/hopper/text?doc=Perseus%3Atext%3A1999.01.0126%3Abook%3D3&force=y
2 COMMENTS
Amazing history
thanks..